የፕሮሴቴት ካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች (Risk factors) የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?

21-01-2026, 07:39 PM

በካንሰር የመያዝ እድልን የሚጨምር ማንኛውም ነገር የካንሰር አጋላጭ ሁኔታ (Risk factor) ይባላል። ለፕሮስቴት ካንሰር ሊያጋልጡ ይችላሉ የሚባሉትን ሁኔታዎች ቀጥሎ እናያለን። ስለነዚህ የካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች ማወቅ ለምን ይጠቅማል ቢባል አንድ ሰው እነዚህ ካንሰር  አጋላጭ  ሁኔታዎች ካሉበት በፕሮስቴት ካንሰር የመያዝ እድሉን ለመቀነስ ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ይረዳዋል። ሀኪም ፊት ቀርቦ ማማከር ካለበትም እንዲያማክር ፍንጭ ይሰጠዋል። ፕሮስቴት ካንሰር የሚመጣው በዚህ ምክንያት ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ቀጥሎ የተዘረዘሩት አጋላጭ ሁኔታዎች ግን በሳይንስ ተጠንተዋል።


1. እድሜ እየገፋ ሲሄድ (Increasing Age)


የፕሮስቴት ካንሰር እድሜያቸው ከ 50 በታች የሆኑ ወንዶች ላይ ብዙሞ አይከሰትም። የወንዶች እድሜ እየገፋ በሄደ ቁጥር ግን በፕሮስቴት ካንሰር የመያዝ እድላቸውም ይጨምራል።


2. ቤተሰብ  ምክንያት (Family History)


አንድ የወንድ ፆታ ያለው ሰው አባቱ ወይም ወንድሙ ወይም ልጁ በፕሮስቴት ካንሰር ታመው የሚያውቁ ከሆነ እሱም በፕሮስቴት ካንሰር የመያዝ እድሉ ከፍ ሊል ይችላል።

 

 


3. በዘር (race) ምክንያት


ከነጮች ይልቅ የጥቁር ዝርያ ያላቸው ወንዶች በፕሮስቴት የመያዝ እድላቸው ይጨምራል ። የእስያ (Asian) ዝርያ ያላቸው ደግሞ በፕሮስቴት ካንሰር ብዙ ጊዜ አይታመሙም።


4. የዘረመል ችግር (Genetic mutation)


ከወላጅ የሚወረስ የዘረመል ችግር ያለበት ሰው በፕሮስቴት ካንሰር ሊያዝ ይችላል። ለምሳሌ BRCA 2 እና BRCA 1 የሚባሉ የዘረመል አይነቶች ላይ ጉዳት (Genetic mutation) ከደረሰባቸው በፕሮስቴት ካንሰር የመያዝ እድልን ይጨምራሉ።


5. ከመጠን በላይ ውፍረት መጨመር (Obesity)


ከመጠን በላይ መወፈር ከሚያመጣቸው ችግሮች መካከል አንዱ ለፕሮስቴት ካንሰር ተጋላጭነትን መጨመር ነው።  መፍትሄው ደግሞ ክብደትን ለመቀነስ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ፣ አመጋገብን ማስተካከል እና በሙያው የሰለጠኑ ሀኪሞችን ማማከር ነው።


6. የሆርሞን መዛበት 


ሰውነታችን ጤናማ ሆኖ እንዲያድግ የሚያደርጉ ሆርሞኖች በሰውነታችን ውስጥ አሉ። ከነዚህ ሆርሞኖች መካከል አንዱ ኢንሱሊን ላይክ ግሮውዝ ፋክተር (Insulin like growth factor) ይባላል። ይህ ሆርሞን ያለ አግባብ የሚጨምር ከሆነ ለፕሮስቴት ካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል።


እዚህ ጋር በጥንቃቄ ልንረዳው የሚገባ አንድ ነገር አለ። ይህም እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች ያለበት ሰው በፕሮስቴት ካንሰር የመያዝ እድሉ ይጨምራል ማለት ነው እንጂ በእርግጠኝነት ወደፊት ካንሰሩ ይይዘዋል ብሎ መደምደም አይቻልም። በዚያው ልክ ደግሞ እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች የሌሉበት ሰው ወደፊት ፕሮስቴት ካንሰር በጭራሽ አይዘውም ማለትም አይደለም። ሊይዘው ይችላል።