ፕሮስቴት ካንሰር (prostate cancer)

21-01-2026, 07:35 PM

ሰላም እንዴት ናችሁ?

በዚህ ፅሁፍ ስለ ፕሮስቴት ካንሰር ወሳኝ የሚባሉ ነጥቦችን እናነሳለን። ፕሮስቴት ካንሰር ምንድን ነው? የፕሮስቴት ካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? ምልክቶቹ እና ህክምናውስ? የሚሉት እና ሌሎች አስፈላጊ ነጥቦችን በሙሉ እንዳስሳለን።


ፕሮስቴት ካንሰር ምንድነው?


በአጭሩ ፕሮስቴት ካንሰር ማለት በፕሮስቴት እጢ(gland) ውስጥ የሚፈጠር የካንሰር አይነት ነው። በአለማችን ወንዶች ላይ ከሚከሰቱ ካንሰሮች ውስጥ ፕሮስቴት ካንሰር በብዛት በመከሰት አንደኛ ደረጃን ይይዛል። በተቃራኒው ደግሞ ሴቶች ላይ በብዛት የሚከሰተው ካንሰር - የጡት ካንሰር ነው። ፕሮስቴት ካንሰር ሴቶች ላይ አይፈጠርም ። ለምን ቢባል ፕሮስቴት የሚባለው እጢ(gland) የሚገኘው ወንዶች ላይ ብቻ ስለሆነ።


ፕሮስቴት እጢ(Prostate Gland) ምንድነው?


ኘሮስቴት ወንዶች ላይ ብቻ የሚገኝ የመራቢያ አካል ነው። አቀማመጡም ከሽንት ፊኛ ዝቅ ብሎ ሲሆን የሽንት መውረጃ ቱቦን (urethra) አቅፎ ይይዛል። ከፕሮስቴት ጀርባ በኩል ደግሞ ሬክተም (Rectum) የሚባለው የትልቁ አንጀት ክፍል አለ።

ፕሮስቴት ስራው ምንድነው?


ፕሮስቴት ስራው ፈሳሽ ማመንጨት ነው - ይህ  ፈሳሽ ከወንድ ስፐርም ሴል ጋር ይቀላቀልና የወንድ ዘር ፈሳሽ (semen) እንዲፈጠር ያደርጋል። ወጣት ወንዶች ላይ ፕሮስቴት መጠኑ 4 ሳ.ሜ * 3 ሳ.ሜ ይሆናል። እድሜ እየገፋ ሲሄድ ደግሞ መጠኑ ሊጨምር ይችላል። የፕሮስቴት መጠኑ ስለጨመረ ግን ሁሌም ካንሰር ነው ማለት አይደለም ምክንያቱም የፕሮስቴት እጢ መጠን ካንሰር ባልሆኑ ምክንያቶችም ሊጨምር ስለሚችል።